ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ታሪካዊ ሊባል የሚችል ቀን ! 

በዛሬው እለት ጥር 30/05/09 ዓ/ም ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ታሪካዊ ሊባል የሚችል ቀን ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በኢትዮጵያ የሙዚቃኞች ማህበር አማካይነት በተጠራው ጉባኤ ላይ ባለሙያዎቹ ከስምምነት የደረሱባቸው ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ላለፉት በርካታ ዘመናት የሙዚቃ ባለሙያዎች ማለትም ድምፃውያን ገጣምያን የዜማ ደራስያን እንዲሁም አቀናባሪዎች በፈጠራ መብት ሊያገኙ ከሚገባቸው ጥቅምና እውቅና ውጭ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለዚህም ምክንያት ተደርገው የቀረቡት በኢትዮጵያ ህገመንግስት የፀደቀው አዋጅ ተግባራዊ ያለመሆኑ እና የጥቂት ራስ ወደዳድ ግለሰቦች ህገወጥ የገበያ ስርአት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  በዚህም የብዙሃኑ ድምፃውያን ገቢ ከእጅ ወደ አፍ እንዲሆን በስራቸው ሊያገኙ የሚገባቸውን እውቅናም ሳያገኙ ዘመናት ተቆጥረው ነበር፡፡

 ዛሬ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በተዘጋጀው ጉባኤ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ማህበራት ጋር በመተባበር ህገወጥ የገበያ ስርጭትን የሚገታና እጅግ ዘመናዊ እና የተደራጀ የፈጠራ መብት ምዝገባ መንገድና የግብይት ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችለውን እቅድ በማቅረብ በብዙሃኑ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሙሉ ድጋፍና ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል፡፡በቀጣይም ይህን የፈጠራ መብት ምዘገባና ቁጥጥር እንዲሁም ዘመናዊ የተባለውን የገበያ ስርአት ሂደትና አፈፃፀም ማህበሩ ተግባራዊ እያደረገ ለህዝብና ለመገናኛ ብዙሃን እንደሚያሳውቁ ተጠቁሟል፡፡ ተጨማሪ የምስልና የድምፅ ግብአቶችን ወደናንተ የምናደርስ ይሆናል፡፡ 

 

ዘጋቢ፡ ገዳም በእውቀት