አባ ኢየሱስ ሞዓ

አባ ኢየሱስ ሞዓ

ወጣቱ ትውልድ በኢትዮጵያዊ ምግባርና ጥበብ ተኮትኩቶ በስጋዊናበመንፈሳዊ ህይወቱ የተሳለ ሰይፍ እንዲሆን  የቀደሙ አባቶችን የህይወት ተሞክሮና ታሪክ መማር እንዳለበት እናምናለን፡፡ እኛም በዚህ ወር እትማችን  አገራችን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው እጅግ  በርካታ ቅዱሳን አባቶች መካከል አንዱ የሆኑትን አባ ኢየሱስ ሞዓን ልናስተዋውቃችሁ ወደድን፡፡

በ1210 ዓ/ም በጎንደር ክፍለአገር ስማዳ ወረዳ ዳህና በተባለው ስፍራ ከአባታቸው ዘክርስቶስና ከእናታቸው እግዚእ ክብራ የተወለዱት አባ ኢየሱስ ሞዓ በ1240 ዓ/ም ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዓ ለሰባት አመታት መነኮሳቱን እያገለገሉ ቅዱሳት መፃህፍትንና መንፈሳዊ ጥበባትን እየተማሩ ከቆዩ በኃላ በ1247 ዓ/ም የደብረዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሀኒ ምንኩስናን ተቀብለዋል፡፡
የአዳም የቅርብ ወዳጅ በሚባል የሚታወቀው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል አባ ኢየሱስ ሞዓ በመንፈሳዊ ህይወታቸው ተግተው ይኖሩ በሚኖሩበት በአንድ ወቅት ተገለፀላቸው፡፡ እንዲህም የሚል መልእክት ነገራቸው “ ገድልህና ትሩፋትህ በዓለም ህዝብ ሁሉ ትተህ የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ እስጢፋኖስ ወደ ተባለው ስፍራ ሂድ “፡፡ አባታችን ቦታውን ስለማያውቁት መላእኩ ቅዱስ ገብርኤል እየመራቸው ከበአታቸው ተነስተው ጉዞ ጀመሩ፡፡ እጅግ በሚደንቅ ሁኔታም በዘመኑ ብዙ ወራት ይፈጅ የነበረውን መንገድ በስድስት ቀን ጨርሰው ከስፍራው ደረሱ፡፡
አባ ኢየሱስ ሞዓ ከስፍራው ከደረሱበት ጊዜ አንስተው መንፈሳዊ ትጋታቸውን በመጨመር በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስትያን ማገልገል ጀመሩ፡፡ አባታችን ቀኑን በአካባቢው የሚገኘውን ህዝብ መንፈሳዊና ምድራዊ ጥበባትና ታሪኮችን ሲያስተምሩ ከቆዩ በኃላ ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ወደሐይቁ በመግባት ለአገር ለወገን ሲፀልዩ ያድሩ ነበር፡፡
ቅዱሱ አባታችን ለአርባ አምስት ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስን አበምኔት ሆነው ገዳሙን አስተዳድረዋል፡፡ በነዚህ ዘመናት ውስጥ ቅዱሱአባታችን አባ ኢየሱስ ሞዓ እጅግ በርካታ የጥበብና የታሪክ መፃሕፍት አዘጋጅተው በገዳሙ አኑረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር እነዚህ በርካታ ሺህ የጥበብና የምስጢር መፃሕፍት ከትውልድ ወደትውልድ እንዲሻገሩ በአገራችን የመጀመርያው ሊባል በሚችል ደረጃ በገዳሙ ቤተመፃሕፍት አቋቁመዋል፡፡  ታሪኩን ተረት ተረት  እያለ ለሚያጣጥለው ይህ ዘመነኛ ትውልድ አባታችን አባ ኢየሱስ ሞዓ አገራችን ኢትዮጵያ የሰባት ሺህ ዘመናት የታሪክና የስልጣኔ  ባለቤት እንደሆነች በሚያስረዱ መፃሕፍት ስብስብ  የመሰረቱት ይህ ቤተመፃሕፍት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡
ትምህርት ለሰው ልጅ መሰረታዊ ነገር እንደሆነ የተረዱት አባታችንበገዳሙ ትምህርት ቤት አቋቁመው  800 የሚሆኑ መነኮሳት በትምህርተ ሀይማኖት አሰልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ መርቀው በመላ አገሪቱ እንዲሰማሩ አድርገዋል፡፡ የእርሳቸው ፍሬ ከሆኑት ታላላቅ መንፈሳዊ ሊቃውንት አባቶች መካከል አቡነ ተክለሃይማኖት( ዘደብረሊባኖስ) አባ ኂሩተ አምላክ( ዘጣና ሐይቅ ) አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አባ ዘኢየሱስ አባ ፀሎተ ሚካኤል አባ አሮን ይጠቀሳሉ፡፡ ከነገስታቱም መካከል አፄ ይኩኖአምላክ በመንፈሳዊ ጥበባትና ታሪኮች የታነፁት በአባታችን አባ ኢየሱስ ሞዓ አማካይነት ነው፡፡
አባታችን አባ ኢየሱስ ሞዓ ለ45 አመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከቆዩ በኃላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ/ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ አባታችን የሰባት ሺህ ዘመናት ታሪካችንን እና የአባቶቻችንን ሰማያዊና ምድራዊ ጥበባት ሳይቆነፃፀሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ ያበረከቱት አስተዋፅዖ ሁሌም ከህሊናችን የማይጠፋ ታላቅ ውለታ ነው፡፡

ምንጭ፡ ገድለ ኢየሱስ ሞዓ

 

 

 

ይከተሉን!