ቴርሞዳይናሚክስ

Thermodynamics በተሰኘው የሳይንስ ዘርፍ ላይ በሚነሱ እውቀቶችና ንድፈ ሀሳቦች ላይ ኢትዮጵያውያን አያቶቼ የራሳቸው እሳቤ፣ እውቀት እና ንድፈ ሀሳብ ሊኖራቸው እንደሚችል ዘርፉ ላይ የተሰሩ ጥናቶችን በተመለከትኩ ቁጥር የማስበው ነው። 

እንደሚታወቀው ይህ የሳይንስ ዘርፍ የሚያጠናው ሀይል እና ሀይል ከተለያዩ ነገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ነው። ጥናቱ በተለያየ ዘርፍ የተከፈለ ሲሆን አንደኛው biological thermodynamics ይሰኛል። ባያሎጂካል ቴርሞዳይናሚክስ ትኩረት የሚያደርገው ደግሞ በሰው ልጅ ውስጣዊ አካል ውስጥ ስለሚፈጠር ሀይልና የአፈጣጠር ሂደቱ ነው። በዋነኝነትም ጥናቱ ATP hydrolysis, protein stability, DNA binding, membrane diffusion እና enzyme kinetics ያጠናል። የኔ ንድፈ ሀሳብ እና ጥያቄ እዚህ ጋር ነው የሚመጣው። የሰው ልጅ ለህልውናው የሚያስፈልገውን ውስጣዊ ሀይል አፈጣጠር፣ ሀይል የማጎልበት ሂደቱ ፣ የሀይል መዛባቱ በሰው ልጅ አካላዊና ስነአእምሯዊ ሁኔታ ላይ ስለሚያሳርፉት ተፅእኖ፣ በሰውነታችን ውስጥ ያለው ሀይል እና ተመጣጥኖ ሊኖር ስለሚገባው ሀይል አያቶቻችን የራሳቸው ምልከታ ነበራቸው ብዬ አምናለሁ። አራቱ የስጋ ባህሪት ተብለው የተቀመጡት እሳት፣ ነፋስ ፣ ውሃ እና አየር ለአካላዊ ሁኔታችን እያንዳንዳቸው የሚያመነጩት ሀይል አለ። የእያንዳንዳንዳቸው ሀይል ከሌላኛው ጋር የሚዛመድበትና አብሮ የሚሰራበት ሂደት አለ። እነኚህ አራት ባህሪያት ስላላቸው ሀይልና አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር ስለሚዛመዱበት ሁኔታ የስነፍጥረት አንድምታ መፅሐፎች ላይ በስፋት የተዘረዘረ እውቀት አለ። ይሄ መፅሐፍ በገበያ ላይ ለመኖሩ እርግጠኛ ባልሆንም የመናገሻ ገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ቤተመፅሐፍት ውስጥ ይገኛል። በተጨማሪ አክሲማሮስ የተሰኘው ስለ ስነፍጥረት የሚያትተው መፅሐፍ ላይ የሚገኙ መረጃዎችም አሉ። በእርግጠኝነት መናገር የምችለው በአራቱ ባህሪያት ኢትዮጵያውያን አያቶቼ የነበራቸው እውቀት ቢፈለቀቅ እና ቢተነተን ከባዮሎጂካል ቴርሞዳይናሚክስ ባልተናነሰ ለሰው ልጅ ህልውና የሚጠቅሙ እውቀቶችን ማበርከት ይችላል። በዚህ ፅሁፍ ማንሳት የፈለኩት እንደወትሮው ሁሉ አገራችን የራሷ የሆኑ ሊተገበሩ የሚችሉ እውቀቶች፣ ሀሳቦች እና ንድፈ ሀሳቦች እንዳሏት ለመናገር ነው። እንደ ምእራቡ አለም የኛ የምንለውን እውቀት እና ሀሳቦች ሳንንቅ ሳንጥል ልናጠናቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። የሚናቅ ሀሳብ የለም። አገራችን የኔ የምትለው የራሷ የሆኑ እውቀቶች አሏት። እኔ ባጎደልኩ እናንተ ሙሉበት። 

#ራፋቶኤል

 

 

 

ይከተሉን!