Christ

#ክርስቶስን የማያውቅ ትውልድ#

"ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። የማር ወ ም8 ቁ27-30 ጌታችንን መድሃኒታችን እየሱስ ክርቶስን እና ከእርሱ የሆኑትንስ ሰዎች የምናውቀው እንዴት ነው? ይህ በዘመናችን እያሳሰበ የመጣ የብዙዎች ጥያቄ ነው:: እየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስሙ እራሱ መድሃኒት የሆነ የተቀባ ንጉስ አልፋና ኦሜጋ በሁሉም ላይ የበላይ የሆነ ማለት ነው:: በዚህ ስም ፍጥረታት ተፈጠሩ: ሰማያት ፀኑ: ደዌያን ተፈወሱ :ይፈወሱማል: ታምራት ተደረጉ: ይደረጉማል:: ነገር ግን አምላክችን ክርስቶስ ከዚህም ሁሉ በላይ ነው:: እርሱ ክርስቶስ ነው:: አምላካችን ክርስቶስን ማወቅ ማለት በግርግርና በውዥንብር መሃከል እንኳ እንደ ጴጥሮስ በጠራ አይን ክርስቶስን ማየትና ማወቅ ማለት ነዉ:: "እናንትስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?" ነው ጥያቄው:: መጥምቁ ዮሐንስ አይደለሁም: ነገር ግን መጥምቁ ዮሐንስ የኔ ነው:: ኤልያስ አይደለሁም: ነገር ግን ኤልያስ የኔ ነው:: ከነብያትም አንዱ አይደለሁም: ንብያት ግን የኔ ናቸው እያለን አይደለምን? አዎን እንደዚያ እያለን ነው:: ነገር ግን የሚያስያዝነው ዛሬም እንደድሮው ክርስቶስን አሳንሰን መጥምቁ ዮሐንስ:ኤልያስ ወይም ነብይ እያልን የምንሳደብ መኖራችን ነው:: ፈጣሪውን ፍጡር ብሎ ከመናገር በላይ ምን ድፍረት አለ:: ዛሬ ክርስቶስን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የተሳነን የክርስቶስ የሆኑትንም እንኳ ለይቶ ማወቅ ተስኖናል:: ዛሬ እገሌ የክርስቶስ ነው ብለን በተናገርንበት አንደበታችን ነግ መልሰን የዲያቢሎስ ነው የምንል መንታ ምላስ ያለን እውሮች ነን:: ክርስቶስን ሳይሆን ታምራትን እያነፈነፍን ወዲያና ወዲህ የምንሮጥ ባቋራጭ ፅድቅን ለማግኘት የምንቀላውጥ ሰነፎች ነን:: እገሌ እንዲህ አይነት ፀጋ አላቸው: እንዲህ ያደርጋሉ: እያልን ትርኢት ለማየት ግር ግር የምንፈጥር: የመንፈስ ቅዱስን ስራ ከአለማዊ ትያትር ተርታ ያሰለፍን ወንጀለኞች ነን:: በዚህ ምክንያት ትክክለኛውን የክርስቶስን ሰው ካልሆነው የምንለይበት አይን እና ልቦና የለንም:: እውነት ነው: እግዚአብሔር አምላካችን ድሮም ዛሬም የመፈወስ: አጋንንትን የማውጣት: የማስተማር: የመዘመር ወዘተ ፀጋ የሰጣቸው አባቶች ነበሩን አሁንም አሉን:: ለመድሃኒዓለም ክብር ምስጋን ይግባው:: የሰማይ የአባታችን ቤት የብዙ ብዙ የፀጋ ክምችት ተትረፍርፎ ያለበት ነው:: እርሱን ላስደሰቱት እንደፈቀደ ይሰጣቸዋል:: ነገር ግን "መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ። " ሉቃ ም10:20 ስላለ: አስቀድመን ስማችን በስማይ የፅድቅ መዝገብ እንዲፃፍ መትጋትን በህይወታችን ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ክርስቶስን የማወቅ: መንገዱንም የማወቅ: የክርስቶስም የሆኑትንም ሰዎች ለይተን ማወቅ የምንችልበት ጤናማ አይን ይኖረናል:: ዛሬ ጤናማ ያልሆነ አይን: ከክፉ ልቦናና ከተሳዳቢ አንደበት ጋራ የተቀዳጀን ጉዶች ስለሆንን ጎራ ጎራ ለይተን እኔ ነኝ የክርስቶስ: እኔ ነኝ የክርድቶስ በሚል ክርክር ተጠምደን የስድብ ዲንጋይ እንወራወራለን:: በእውኑ ክርስቶስ በዚህ ተግባራችን የሚደሰት ይመስለናል እን? ዲያቢሎስም ይህን መንገዳችንን ወዶት: ቅን የሆኑትንም የቤተ ክርስቲያን ልጆችን እና የቤተ ክርስቲያን አባቶችን: በተለያዮ መድረኮች በሃሰት እየወነጀለ ያለ ስማቸው ስም ሰጥቶ: እርሱን አጥብቀው የሚቃወሙትን "የኔ ናቸው" ሲለን ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ አፋችንን አሹለን በመሳደብ የብዙዎችን ቅን የሆኑ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ቅስም የሰበርን ምን ያህሎቻችን ነን:: ዛሬ በርትተው ክርስቶስን ስላገለገሉ አክብሩን ሳይሉን እኛ እራሳችን በውዳሴ ከንቱ ሆይ ሆይታ እላይ እንሰቅላቸውና ነገ ደግሞ መልሰን "እረ እንዲህ ናቸው አሉ" እንልና ከመሬት እንከሰክሳቸዋለን:: ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በምድር እያስተማረ እና እየፈወሰ በሚመላለስበት ጊዜም እንኳ ግር ግር እየፈጠሩ የሚጋፋት: ትያትር የሚናፍቁ የነበሩት ሰዎች ብዙዎች ነበሩ:: ነገር ግን በእምነት ዉደሱ የተጣሩ እና የቀረቡ: በጠራ አይንም ክርስቶስን ያዮ "እርሱ ክርስቶስ ነው" ያሉ ጥቂቶች ነበሩ:: ሰለዚህ ከሁሉ በፊት በዕምነት ክርስቶስን ለማየትና ክርስቶስን ለማወቅ እንጣር:: ወስብሃት ለእግዚአብሔር!!!

#ኤሶፕ ኢትዮጵያ

 

 

 

ይከተሉን!